• An Image Slideshow
 • An Image Slideshow
 • An Image Slideshow
 • An Image Slideshow
 • An Image Slideshow
 • An Image Slideshow
 • An Image Slideshow
 • An Image Slideshow
 • An Image Slideshow
 • An Image Slideshow
 • An Image Slideshow
 

ማቲዎስ ማነው?

ማቲዎስ ከእናቱ ወ/ሮ አምሳለ በየነና ከአባቱ አቶ ወንዱ በቀለ ሰኔ 9 ቀን 1991 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰዓት በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደ፡፡ የሁለተኛ ዓመት ልደት በዓሉን ባከበረ ጥቂት ቀናት ውስጥ በቤተሰቡ ዘንድ በፍፁም ያልተጠበቀ የጤና ችግር አጋጠመው። በጥሩ ሁኔታ ዕድገቱን ጠብቆ በመኖር ላይ የነበረውና አንድም ቀን ህመም አጋጥሞት የማያውቀው ማቲ በተደረገለት የጤና ምርመራ በደም ካንሠር ህመም መያዙ ታወቀ።


ዝርዝር ንባብ...
 
Amharic (Ethiopia)English (United Kingdom)

ጤናማ ህይወት

PDF ፕሪንት ኢሜይል

የመመሪያው አጠቃቀም

በመመሪያው ውስጥ ከተጠቀሱት መካከል አንዳንዶቹን አስቀድመው እየተጠቀሙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ወሳኝ ለውጥ ለማምጣት ከፈለጉ፡-
 • በመመሪያው ውስጥ ከተጠቀሱት መካከል ከተቻለ ሁሉንም ካልተቻለ የተወሰኑትን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ያድርጉ፣አጀማመርዎ ቀስ በቀስ ይሁን፤ በመጠነኛ  ጥረት ደረጃ በደረጃ ወደ ክፍተኛ ለውጥ እንደሚያደርስዎ ይገንዘቡ፡ጤናማ የአኗኗር ሥርዓትን በሚኖሩበት ቀበሌ፣ የሥራ ቦታ ወይም ት/ቤት ውስጥ እንዲዘወተር የበኩልዎን አስተዋፅኦ ያድርጉ፣በራስዎ ላይ  የሚፈልጉትን ለውጥ ለማምጣት  ምቹ ሁኔታን ይፈጥርልዎታል፡፡
ጤናማ ክብደት ያለዎት መሆኑን አይዘንጉ፣

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአለማችን በአብዛኛው በተለይ ደግሞ በአገራችን ውፍረት የምቾትና ደህንነት ምልክት ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡እንዲያውም አንድ ሰው ወፍሮ ከታየ  አምሮበታል' ተመችቶታል ይባላል፡፡ውፍረትን በራሱ እንደ ህመም አድርጎ መቁጠር ትክክል ባይሆንም ከሚያስፈልገው በላይ ክብደት መኖር በተለይ ተላላፊ ላልሆኑ ህመሞች መከሰት ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ ታውቋል፡፡በአንድ ታዋቂ የትምህርት ተቋም ተካሂዶ ይፋ ባልወጣ ምርምር ውጤት መሠረት ከአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ 30% ክብደታቸው ከሚፈልገው በላይ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ይኽ እንግዲህ የአዲስ አበባ ነዋሪ ክብደቱን በመቆጣጠር ረገድ አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የሚያስገነዝብ ነው፡፡
ክብደትዎን ለመቆጣጠር እንዲረዳዎ
 • የሚወስዱትን የካሎሪስ መጠን ከአካል እንቅስቃሴዎ ጋር ያገናዝቡ ወይም ያጣጥሙ፣
 • በአጠቃላይ በሕይወት ዘመንዎ አላስፈላጊ የሆነ ክብደት መጠን  እንዳይኖርዎ ጥረት ያድርጉ፣
 • በአሁኑ ወቅት ከሚፈለገው በላይ ክብደት ካለዎት ተመጣጣኝ ክብደት  እንዲኖረዎ ጥረት ያድርጉ፣
ትክክለኛውን የክብደት መጠን እንዴት ማወቅ ይቻላል?

የሚያስፈልገዎትን የክብደት መጠን ለመወሰን የተለያዩ አማራጮች ቢኖሩም የሰውነትዎን ክብደት መጠን ማስላት (Calculating your body mass index-BMI) ከሁሉም የተሻለ ነው ተብሎ ይገመታል ፡፡ ይህም ስሌት የክብደትዎን መጠን ከቁመትዎ መጠን ጋር በማነፃፀር የሚገኝ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ቁመትዎ 1 ሜትር ከ70 ሣንቲ ሜትር ቢሆን ሊኖርዎት የሚገባው ጤናማ ክብደት 70 ኪሎ ግራም  ነው ፡፡ ክብደትዎ ከዚያ በላይ ከሆነ አስፈላጊ አይደለም ማለት ነው፡፡ የአሰላሉን ስርዓት ይበልጥ ለመረዳት ሐኪሞን ማማከር ወይም የአሜሪካ ካንሠር ሶሳይቲ ድህረ ገፅ www.cancer.org ማየት ይችላሉ ፡፡  በአሁኑ ጊዜ ጤናማ ክብደት መያዝ ከምንጊዜውም የበለጠ ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ትክክለኛውን ዓይነት ምግብ መመገብና የአካል እንቅስቃሴ ማዘውተር ለክብደት ቁጥጥር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ፡፡

ክብደትን መቀነስ (Down Size)

የማያስፈልግዎትን ክብደት ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግና ቆራጥነትን ይጠይቃል ፡፡ ይህን ዓይነት ቆራጥ እርምጃ ለመውሰድ የተለያዩ አማራጮች አሉ፤ ከእነሱም መካከል የሚቀርብልዎትን ምግብ ከሰው ጋር ተካፍለው መመገብ፣ ወይም ግማሹን  ዛሬ  የተቀረውን እንዳይበላሽ በአግባቡ አስቀምጠው ነገ መመገብ፡፡ እንደዚህ ያሉ ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን ውጤታማ እርምጃዎች ተዳምረው ከፍተኛ የካሎሪና የክብደት  ቅነሳ ለማድረግ ይረዱዎታል ፡፡

የታሸገ ምግብ የሚመገቡ ከሆነ በምግቡ መያዣ ላይ የተፃፉትን በሚገባ ያንብቡ

ዝቅተኛ ስብ ወይም ከስብ የነፃ የሚለው አባባል ሁልጊዜም ዝቅተኛ ካሎሪ ያለው ነው ማለት አይደለም ፡፡ ዝቅተኛ ስብ ያላቸው ምግቦች ከስኳርና ከካርቦንሃይድሬት ከፍተኛ ካሎሪን የሚያገኙ ስለሆነ ክብደትዎን ለመቀነስ ላይረዱዎት ይችላሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ የአትክልት፣ ፍራፍሬና ያልተፈተጉ (Whole grain) ምግቦች ለመተካት ጥረት ያድርጉ፡፡

ቀልጣፋ የሆነ የአካል እንቅስቃሴ ላይ የተመሠረተ አኗኗር ይከተሉ

በአገራችን ባልተለመደና ባልተጠበቀ አኳኋን የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ እንደሆነ ታውቋል ፡፡ በዚህም በተለይ በከተማ ውስጥ በቅርብ ርቀት ሳይቀር ተሽከርካሪ የመጠቀም አዝማሚያ ይታያል ፡፡ ይህ ደግሞ የከተማውን ትራንስፖርት ፍላጐት ከማባባሱና ከማሳደጉም በላይ በጤና አጠባበቅ ረገድ ከፍተኛ ተፅዕኖ  በማድረግ ላይ ይገኛል ፡፡ በበለፀጉ አገሮች ዋና ዋና ከተሞች እንደ ፓሪስና አምስተርዳም ባሉ ከተሞች የአካል እንቅስቃሴን ጥቅም በመረዳት ብስክሌት መጠቀም በከፍተኛ ደረጃ እየተዘወተረ ከመገኘቱም በላይ አማራጩን ምቹ በሆነ ሁኔታ ለመጠቀም እንዲቻል የከተማ ውስጥ መንገድ ሥራን ፕላን እንደገና በማጤን ላይ ይገኛሉ፡፡ 
የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም በቂ የሆነ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ ጤናዎን በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርግ መሆኑን ጠንቅቀው መረዳት ይኖርብዎታል ፡፡ ስለሆነም በሥራ ቦታዎ ላይ በየትኛውም የኃላፊነት ቦታ ላይ ቢመደቡ ሁኔታው እስከፈቀደ ድረስ በተላላኪ ከመጠቀም ይልቅ እራስዎ ቢንቀሳቀሱ ለጤናዎ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል ፡፡ አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ለእግር ጉዞ ቅድሚያ መስጠት ይጠቅምዎታል፡፡ 
ትላልቅ ሰዎች (Adults)

በየዕለቱ ከሚሠሩት ሥራ በተጨማሪ ከመካከለኛ ተነስቶ የተለያዩ ጠንከር ያለ የአካል እንቅስቃሴ  ቢያንስ የ30 ደቂቃ ያህል ማድረግ ይኖርብዎታል ፡፡ በየዕለቱ ከሚሠሩት በተጨማሪ በየሳምንቱ አምስት ቀናት ከ45 እስከ 6ዐ ደቂቃ የሚወስድ እንቅስቃሴ ማድረግ ጥረቱን የበለጠ    ውጤታማ     ያደርገዋል፡፡
ህፃናትና ታዳጊዎች ( Children & Adolescents)

ከመካከለኛ  ጠንከር እያለ የሚያድግ በሳምንት  5 ቀናት በየዕለቱ ቢያንስ 60 ደቂቃ የአካል  እንቅስቃሴ     ማደረግ ይጠቅማል፡፡ 
እየተዝናኑ የአካል ብቃትዎን ደረጃ ያሳድጉ

የአካል እንቅስቃሴ ሲባል ስፖርት መሥራት ብቻ አይደለም ፡፡ እየተዝናኑ የእግር ጉዞ ማድረግ ፣ ውሃ ዋና መዋኘት  በግቢዎ ወይም በሥራ ቦታዎ  አትክልት መኮትኮት ፣ የቤት ውስጥ ሥራ መሥራት' ( ቤት ማፅዳት፣ ምግብ ማብሰል፣ አልጋ ማንጠፍ፣ ልብስና ዕቃ ማጠብ፣  ዳንስ መደነስ ወይም እስክስታ መጫወት፣) እነዚህንና ሌሎችን እንቅስቃሴዎችን ማዘውተር እጅግ ጠቃሚ ናቸው ፡፡ ልጆች ካለዎት ደግሞ ከልጆችዎ ጋር አብረው ቢሠሩ ሂደቱን ማራኪ ያደርግዋል ፡፡በተጨማሪ በየዕለቱ ለ 20 ደቂቃ ያህል የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ በጣሙን ጠቃሚ ይሆናል፡፡
የእፅዋት ተዋፅኦ ላይ ያተኮረ ጤናማ ምግቦችን ይመገቡ፣

በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የተነሳ የተሟላና ሁሉንም የምግብ ዓይነት መመገብ ብዙም አልተለመደም፡፡በዚህን ምክንያት በኢኮኖሚ የተሻለ ደረጃ ላይ ያለ ኅብረተሰብ ትኩረቱ ሥጋና ቅቤ በመሳሰሉት ላይ ሲሆን አቅሙ ደከም የሚለው ደግሞ በሽሮ ላይ ነው፡፡ስለዚህ ለአመጋገባችን መጓደል ምክንያት የሆነው የኢኮኖሚያችን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ስለምግብ ያለን ግንዛቤ በቂ አለመሆኑም ጭምር  ነው፡፡
 የተሟላ አመጋገብ ማለት ለሰውነታችን የተለያየ አገልግሎት የሚሰጡና ከተለያዩ የምግብ ክፍሎች የሚገኝን ምግብ መውሰድ ማለት ነው፡፡ይሄውም ኃይል ሰጪ ' ሰውነት ገንቢና በሽታ ተከላካይ ብለን መክፈል ይቻላል፡፡ በዚህም መሰረት በኢኮኖሚ ጠንካራ የህብረተሰብ ክፍል ትኩረቱ ስጋ ቅቤና የመሳሰሉት ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑና እነዚህም ምግቦች ሰውነት ለመገንባትና ኃይል ለመስጠት ብቻ የሚያገለግሉ በመሆናቸው ብቻቸውን ያልተሟሉ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህም ለበሽታ ተከላካይና በሰውነታችን ውስጥ ለሚፈፀሙት ክንውኖች እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ቫይታሚንና ሚኔራሎች ጉድለት ይታያል፡፡
በመሆኑም በምግቦቻችን ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ውጤቶች መኖር ከዚህ እንፃር ያለውን  የአመጋገብ ክፍተት ይሸፍናል፡፡    
አመጋገብዎ ለጤና አጠባበቅዎ አስተዋፅኦ ማድረግ ይኖርበታል

እንዳይጠራጠሩ ከአትክልት፣ ፍራፍሬና ያልተፈተጉና ያልተፈበረኩ ምግቦችን አዘውትሮ መብላት ጤናማ ህይወት እንዲኖርዎት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ በካንሠርና በሌሎች ተላላፊ ካልሆኑ ህመሞች ማለትም ስኳር፣ ደም ብዛት፣ የልብ ህመም ወዘተ. የመያዝ ዕድልዎን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ በአንድ ጊዜ ብዙ መጠን ያለው ምግብን ከመመገብ ይልቅ በአነስተኛ መጠን በቀን አምስት ጊዜ መመገብ ጠቀሜታ አለው፡፡
ማጠቃለያ

የምግብ ፍላጐታቸውን ሙሉ በሙሉ ማርካት ባልተቻለባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ውስጥ የሚበላውን የምግብ ዓይነትና መጠን ላይ ትኩረት ማድረግ ትንሽ እንደ ቅንጦት ሊቆጠር ይችላል ፡፡  ነገር ግን የምግብ ፍላጐታችንን ለማሟላት የሚደረገው ጥረት በአንድ በኩል ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ሲሆን በሌላ በኩል  በከተማ አካባቢዎች በከፍተኛ ደረጃ በመስፋፋት ላይ ያሉ እንደ ካንሠር ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ከወዲሁ መበረታታት ይኖርበታል፡፡      
 በመግቢያው ላይ እንደተገለፀው እኛ የሰው ልጆች አፈጣጠራችን በዚህ ምድር ላይ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ለመቆየት ነው፡፡ ይህን አጭርና ውድ የሆነ ጊዜ በአግባቡ ተጠቅመን ጤናማና ደስተኛ መሆን ይገባናል ፡፡ እንደሚታየው ህይወትዎን በሰላምና በደስታ ለመኖር ዋናው ቁልፍ ጤናማ መሆንዎ ስለሆነ ጤናዎን ለመጠበቅ ደግሞ አስቀድሞ መከላከሉ ላይ ማተኮር ይበልጥ ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል ፡፡ 
ጤናዎን ለመጠበቅ የሚደረገው ጥረት በአስቀድሞ መከላከሉ ላይ እንዲያተኩር ማድረጉ በጊዜም ሆነ በወጪ ረገድ ቀላል መሆኑ ብቻ ሳይሆን ይበልጥ ውጤታማም ነው ፡፡ በተግባር እንደሚታየው ተላላፊ ባልሆኑ ህመሞች ከተያዙ በኋላ ከህመሙ ለመዳን የሚደረገው ጥረት ውድና እንደሚታሰበው ውጤታማም አይደለም ፡፡ ጤናማ ሳይኮን የደስታ ህይወት መምራት ስለማይቻል ባለዎት አጭር ጊዜ ተዝናንተውና ተደስተው ለመኖር ለህይወትዎና ጤናዎ ቅድሚያ ትኩረት ይስጡ፡፡ ሶሳይቲያችንንም ለህይወትዎና ለጤናዎ ቅድሚያ እንዲሰጡ አበክሮ ያሳስባል !   በተረፈ ለህይወትዎና ጤናዎ ቅድሚያ ትኩረት ለመስጠት አብረን እንሥራ!፡፡
ለህይወትዎና ለጤናዎ ቅድሚያ ይስጡ!

 
PDF ፕሪንት ኢሜይል

ጤናዎን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ምርጫ አለዎት!

የሰው ልጅ አፈጣጠሩ በዚህ ምድር ላይ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እንዲኖር ተደርጐ ነው ፡፡ ይህ ጊዜ ደግሞ ረዥም ይመስላል እንጂ አጭር ነው ፡፡ ይህን አጭርና ውድ የሆነ ጊዜ በረባው ባልረባው ሳናባክነው በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ፡፡ ይህን ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀም ከሚያስችሉን አማራጮች ለጤናችን ቅድሚያ መስጠት አንዱና ዋነኛው ነው ፡፡  ያሰቡትንና ያቀዱትን ለመፈፀምና ህይወትዎን በደስታ ለማሳለፍ የተሟላ ጤና ያስፈልግዎታል ፡፡ የተሟላ ጤና እንዲኖርዎ ለማድረግ ደግሞ አስተማማኝ ምርጫ አለዎት ፡፡ 

ህመም በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ሊከፈል ይችላል፡፡ አንደኛው ተላላፊ የሚባሉት ሲሆኑ ኤች አይቪ ኤድስ 'ሳንባ ነቀርሳና ወባ የመሣሠሉትን እንዲሁም ተላላፊ  ያልሆኑ የሚባሉት ደግሞ ስኳር 'ደም ብዛት'ልብ ህመምና ካንሠር የመሣሠሉትን ያጠቃልላል፡፡ ሶሳይቲያችን የፈጣሪ መልካም ፈቃድ እንደተጠበቀ ሆኖ  እራስዎን ተላላፊ ካልሆኑ ህመሞች ለመከላከል የሚረዳዎት እጅግ ጠቃሚ አማራጭ አቅርቦልዎታል፡፡ 

እውነት ነው ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትና በቂ የሆነ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ ካንሠርንና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞችን ለመከላከል ይረዳል ፡፡ ከቁመታችን ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ክብደት እንዲኖረንና  ተገቢውን የአካል እንቅስቃሴ በማድረግ /በእግር መጓዝና ስፖርት መሥራት / ጤናማ የአመጋገብ ስርዓት በመከተል /አትክልትና ፍራፍሬን በብዛትና ስጋና ስብ ያላቸውን በመቀነስ/ ካንሠርና ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞችን ለመከላከል ይረዳል ፡፡ አመጋገብዎን በመቆጣጠር ረገድ ጠንቃቃና ብልህ መሆን ይጠበቅብዎታል ፡፡ይህ በቀላል አቀራረብ የተዘጋጀው  የካንሠርንና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል  መመሪያ (Guideline) ጤናን በአስተማማኝ  ሁኔታ ለመጠበቅ  በመላው ዓለም ውጤታማነታቸው የተመሰከረላቸውን እጅግ ጠቃሚ አማራጮችን ያጠቃልላል፡፡

 
 

በራስዎ ተጠቃሚ ስም እና የሚስጥር ኮድ ይግቡ

ማን መስመር ላይ አለ?

አለን 27 እንግዳ መስመር ላይ
 
 
Joomla 1.5 Templates by Joomlashack